- Y
- A

Save Abu Gebre Keto's Life
0% complete
$15,463 raised of
165 donations
ሁለገቡ ባለሞያ፥ አቶ አቡ ገብሬ ኬቶ፥ በአዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ተወልዶ፥ ገና በልጅነቱ በሙዚቃ ፍቅሩ እና ተሰጥዖው ምክንያት ከህፃናት እና ወጣቶች ቲያትር፣ ወደ ኢትዮጵያ ሰርከስ፣ ከሀገር ፍቅር ቲያትር ባልደረባነት እስከ ባላገሩ አይድል የዋሽንት ፈርጥነት፥ እንዲሁም በአገራችንና በዓለም ዙሪያ ታዋቂና አንጋፋ የሆኑ ሙዚቀኞች ስራዎችን በማጀብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረገ ድንቅ የሙዚቃ ሰው ነው።
አቡን ከሌሎች ሙዚቀኞች የሚለየው እና "ሙሉ ባንድ" የሚል ቅፅል ስም ያሰጠው፥ ክራርን፣ ማሲንቆን፣ ከበሮን፣ ጊታርን ወዘተ... በተለየ ሁኔታ ደግሞ ዋሽንትን ይጫወታታል ሳይሆን፥ ይራቀቅባታል ቢባል ማጋነን አይሆንም። አቡ ልዩ ድምፃዊም ነው፥ በተለይ በማሲንቆው ዘለሰኛን፥ አሳድገሽኛል ኢትዮጵያን፣ ዋሽንቱ እያስረቀረቀ ኑኑዬ ጨቅላ ሳይሽን፥ ቦክስ ጊታር እየተጫውተ ደግሞ የመስፍን አበበን፣ የአብተው ከበደን፣ የጋሽ ጥላሁንን፣ የጋሽ ማህሙድን እና የሰይፉ ዮሀንስን የሙዚቃ ስራዎች ሲያዜም፥ በውስጡ ያለውና ተጠልቆ የማያልቅ የሙዚቃ ክህሎቱ በጉልህ የሚታይ የአገር ሀብት ነው።
አቡ ኢትዮጵያ እያለም ሆነ፥ ቶሮንቶ፤ ካናዳን መኖሪያው ካደረገበት ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መዘምራን ጋርም ሆነ ታዋቂ ከሆኑ ዘማሪያን ጋር በሰንበት ከማገልገል አልፎ በብዙዎቹ ዘማሪዎች መዝሙሮች ላይ በሙያው እገዛ በማድረግ አሻራውን ያሳረፈ፥ በርካታ ወጣቶችን ያበቃ ባለሞያም፥ መምህርም ነው።
አቡ ገብሬ ያጋጠመውን ህመም ዋጥ አድርጎ፥ June 20, 2026 ለሰኔ ሚካኤል ንግስ እንደወትሮው ለማገልገል ማሲንቆውን ተሸክሞ ከቶሮንቶ ወደ ሚሲሳጋ ከተማ በህዝብ ማመላለሻ ተሳፍሮ፥ እንደምንም የሚሲሳጋው ሚካኤል ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቢደርስም ህመሙ ሲፀናበት እና አቅም ሲያንሰው የተመለከቱ ምዕመናንና አገልጋዮች በአጣዳፊ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ሆስፒታል ወስደውት፥ ሆስፒታሉ ከአቅሜ በላይ ነው በማለት ወደ ከፍተኛ ሆስፒታል ያሸጋግረዋል። የፅኑ ህሙማን ማቆያ ውስጥ እንዳለ ሁለት ግዜ ከፍተኛ የልብ ድካም ያጋጥመውና ለህይወቱ አስጊ በመሆኑ በአየር ተሳፍሮ ወደ ቶሮንቶ እንዲዘዋወር ይወሰናል።
በዚህ መሃል ኢትዮጵያ ያሉት ባለቤቱ፥ ልጆቹና እህቱ ጉዳዩን በመጠኑ እንዲያውቁት ተደረገና፥ ከጎኑ በነበሩት ጓደኞቹ፥ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ማህበር የአደጋ ግዜ ተጠሪዎች ርብርብ ቶሮንቶ ጀነራል ሆስፒታል ከተዛወረበት ግዜ ጀምሮ፥ ምሽቱን ከፍተኛ ቀዶ ጥገና ተደርጎለት የልቡን ተግባር በ2 ማሽኖች ተተክቶ፥ ወደ 18 ዓይነት የተለያዩ ፈሳሽ መድሃኒቶች እና በ3 ከባድ ማደንዘዣዎች ለ10 ቀናት ኮማ ውስጥ ሆኖ ራሱን ሳያውቅ ልቡን እንዲያሳርፍ ካደረጉ በኋላ፥ ከኮማው አንቅተውት በ2 ነርሶች 24 ሰዓት እየተጠበቀ ትንሽ ማገገሙን ሲያዩ ሰዎች በየተራ ሊጠይቁት የሚችሉበት ትንሽ ቁጥጥሩ የቀነሰ ፅኑ ማቆያ ተዛውሮ ከሰነበተ በኋላ፥ ለ3 ወራት እዛው ቶሮንቶ ጀነራል የሚገኝ የልብ ህሙማን ማዕከል አልጋ ላይ ሆኖ የተለያዩ የህክምና አማራጮችን ሲሞክሩ ከቆዩ በኋላ፥ ከዚህ በኋላ ምንም ማድረግ አንችልም ብለው October 12, 2026 ወደ ሳኒብሩክ ሆስፒታል ፓሌቲቭ ኬር አዛውረውታል።
በመሆኑም ላለፉት 2 ሳምንታት በዚህ ፓሌቲቭ ኬር ውስጥ ይገኛል። ቤተሰቦቹን ወደ ካናዳ ፕሮሰሳቸው ተፋጥኖ እንዲመጡ፥ ካናዳ በሚገኙ የአቡ ወዳጆችና ጓደኞች ለዚሁ ፕሪሰስ ማስኬጃ በሚል ገንዘብ ተዋጥቶ እና ጠበቃ ተቀጥሮ ይሄው ፕሮሰስ ተጀምሯል።
ፕሮሰሱን ለማፋጠንም ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት፣ ከፓርላማ ተወካዮች ቢሮ፥ ከኢትዮጵያ ማህበር፣ ከሙዚቃ ማህበራት እና ከቶሮንቶ ጀነራል ሆስፒታል ሰርጅን እና ሶሻል ወርከር፥ የድጋፍ ደብዳቤዎች ተፅፈው የቤተሰቡ ስፖንሰርሺፕ እንዲፋጠን በርካታ አማራጮች እየተሞከሩ ነው። እስካሁን ለተደረጉት ያልተቋረጡ የህብረትም ሆኑ የግል ፀሎቶች፥ በጎ ተግባራት፥ የካህናት ጉብኝት እና ቡራኬ፣ የማህበረሰባችን ለጋስነት በአቡ እና በቤተሰቡ ስም ከልብ እናመሰግናለን። ቸሩ መድሃኒዓለም ብድራችሁን በበጎ ይክፈላችሁ።
በአሁኑ ሰዓት በቶሮንቶ እና አካባቢው እንዲሁም በመላው ዓለም ወደምትገኙ የአቡ የቅርብ ወዳጆች፥ የሙያ አጋሮቹ፣ እንዲሁም መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንን የምንጠይቀው፥ አቡ ቤተሰቡን በቻለው አቅሙ ሲያግዛቸው እና በገንዘብም ሲደግፋቸው የቆየ ቢሆንም፥ ላለፉት 4 ወራት ሆስፒታል አልጋ ላይ ከዋለ በኋላ፥ የእሱ ቀጥተኛ ድጋፍ ተቋርጦባቸዋል። በተለይ 2 ትንንሽ ልጆቹ ገና ተማሪዎች ናቸው። ስለዚህም፥ እኒህን የአገር ባለውለታ ልጆች መደገፍ እና አይዟችሁ ማለት ከእኛ ይጠበቃል።
ከሁሉም በላይ አጣዳፊ የሆነው ግን አቡ ህይወት አድን የልብ ንቅለ ተከላ እንዲደረግለት እንደ ቅድመ ሁኔታ የተጠየቀው የቅርብ ቤተሰብ የሆነ ሰው ከጎኑ እንዲገኝ እና 24 ሰዓት ክትትል የሚያድርግለት የህክምና ረዳት መኖር ስላለበቸው፥ ይህንና ተያያዥ ውጪዎችን ለመሸፈን የወዳጅ ዘመዶቹ የገንዘብ እርዳታ በአፋጣኝ ያስፈልገዋል።
ይህንን ህይወት አድን ዘመቻ እንድትደግፉ በፈጣሪ ስም እንጠይቃለን። በእዚህም ጥረታችን እንደማታሳፍሩን በማመን የጎፈንድ ሚ አካውንት ከፍተናል። ገንዘቡ ሲፈለግ በ2 ሰው ፊርማ ብቻ እንዲወጣ ታቅዶ ለዚሁ ጉዳይ የሚውል አዲስ አካውንት ከፍተናል። እናንተም የበኩላችሁን እርዳታ ከለገሳችሁ በኋላ፥ ለሌላ መልካም አሳቢ ወገን እንዳታስተላልፉት በትህትና እንጠይቃለን። ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረገው የድጋፍ ማሰባሰቢያ በቀጣይ ዝርዝሩን እናሳውቃለን። ስለ ጊዜያችሁ እና ስለ መልካም ትብብራችሁ ከልብ እናመሰግናለን፥ ክብር ይስጥልን!
ባንቺ እና ፋሲካ
ቶሮንቶ ካናዳ




