Main fundraiser photo

የበረከት ጥሪ! የኢ.ኦ.ተ.ቤ ገዳም በአውሮጳ በመመሥረት አሻራችንን እናስቀምጥ!

Donation protected
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
------------------------------------------------------------------------

ኑ! በጋራ የኢትዮጵያን ገዳም
በምድረ አውሮፓ እናቋቁም


“ምድሪቱንም በየወገኖቻችሁ በዕጣ ትወርሳላችሁ፤ ለብዙዎች እንደ ብዛታቸው ለጥቂቶቹም እንደ ጥቂትነታቸው መጠን ርስትን ትሰጣላችሁ።” (ዘኁ. 33፤54)

በመላው ዓለም የምትገኙ ክቡራንና ክቡራት ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ፣

ከኹሉ አስቀድመን ሰላመ እግዚአብሔር ከኹላችንም ጋር እንዲኾን እንመኛለን። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በውጭው ዓለም ካሏት አህጉረ ስብከት አንዱ የኾነው የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የተሰጡትን ተልእኮዎች ሲወጣ ቆይቷል። አኹንም እየተወጣ ይገኛል። ከእነዚህም ውስጥ በአካባቢው በስደትና በልዩ ልዩ ምክንያት የመጡት የቤተ ክርስቲያን ልጆች በየአካባቢያቸው የቤተ ክርስቲያናቸውን ድምጽና ሙቀት እንዲያገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ማቋቋም፣ አበው ካህናትን አሰማርቶ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ፣ በአካባቢው ተወልደው የሚያድጉ ሕጻናት በየአጥቢያቸው በቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሥርዐት ተኮትኩተው እንዲያድጉ፣ ነገ ቤተ ክርስቲያናቸውንም ይረከቡ ዘንድ ማዘጋጀት፣ በአካባቢው ላለውና ተቀብሎ ለሚያኖረን ሕዝብም የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ድምፅ በማስማት ወደ ዕቅፏ እንዲገባ ማድረግ፣ ወዘተ. የሚሉት ይገኙበታል።

ጊዜያዊ መንበረ ጵጵስናው በበርሊን ደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ያደረገው ሀገረ ስብከታችን በሥሩ ጀርመንን፣ ኦስትሪያን፣ ኔዘርላንድን፣ ስዊዘርላንድን እና ፖላንድን የያዘ ሲሆን 42 አጥቢያዎች፤ 95 በመደበኛና በበጎ ፈቃድ የሚያገልግሉ ካህናትና ዲያቆናት፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናንና ምእመናት አሉት። ወደ አካባቢው የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ፣ ከእነሱ አብራክ የሚገኙ ሕጻናትም በቁጥር እየጨመሩ ይገኛሉ። ይህ የሚወለዱ ልጆች በቁጥር መጨመር የማስደሰቱን ያህል፤ ቤተ ክርስቲያን ያለምንም መሳቀቅ ልጆቿን እየሰበሰበች የምታጠምቅባቸው፣ የምታስተምርባቸው፣ ለታመሙት ፈውስን ላዘኑት መጽናናትን የምትሰጥባቸው፣ ሲያርፉም አስፈላጊውን ጸሎት አድርጋ የምትሸኝባቸው፣ ክቡር ሥጋቸውንም የምታሳርፍባቸው ቦታዎች እንደሚያስፈልጓት የሚያሳስብ እውነታ ነው። በሀገረ ስብከታችን ሥር ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን ፍላጎቶች ለመመለስ በተናጠል የሚያደርጓቸው ጥረቶች እንዳሉ ኾነው፤ ኹሉም በጋራ የሚሰበሰቡበት አንድ ማእከላዊ ቦታ እንደሚያስፈልግ በመታመኑ፤ ሀገረ ስብከታችን ሰፊ ቦታ ገዝቶ አንድ ማእከላዊ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል።

የእስራኤል መፍረስ፣ የሕዝቡም መበተን ያሳሰበው ነሕምያ “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን” (ነህ. 2፤20) እንዳለ ቤቱን በደሙ መሥርቶ በሰጠን አምላክ እርዳታ አምነን የጀመርነው ቦታ የማፈላለግ እንቅስቃሴ ፍሬ ሊያፈራ ከአካባቢው አልፎ በመላው አውሮጳ ብሎም ዓለም ለሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን መኩሪያና መጠጊያ የሚኾን ሰፊ ቦታ በሀገረ ጀርመን ኖርድሃይን ቬዝትፋለን ግዛት ሙንስተር ከተማ አቅራቢያ አግኝተናል። ይህ ቦታ ቀድሞም በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በገዳምነት ተመሥርቶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ፣ በአጠቃላይ 17,400 ካሬ ሜትር ይዞታ ያለው፣ በሀገራችን እንዳሉ ገዳማት በእርሻ መሬትና ትላልቅ ዛፎች የተከበበ፣ ትልቅ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ፣ በርካታ ማረፊያ ክፍሎችና መሰብሰቢያ አዳራሾች ያሏቸው ሕንፃዎች እንዲሁም መካነ መቃብር ያሉት ቦታ ነው።

“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር፣ የጽሙና፣ የትምህርት፣ ጥናትና ምርምር ተቋም በጀርመን” ብለን የምንሠይመው ይህ ታላቅ ቦታ፤ ስሙ እንደሚገልጠው ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የሚመሠረት ነው።ተቋሙ በሥሩ አምስት ማ እከላትን እንዲይዝ ተደርጎ የታቀደ ሲኾን፤ ከመንበረ ጵጵስናነት በተጨማሪ፤ ካህናት፣ ምእመናንና የቤተ ክርስቲያኗን ጥልቅ ዕውቀት፣ ሥርዐትና ትውፊት ማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ ትምህርትና ሥልጠናዎች የሚያገኙበት ይሆናል።በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ አካባቢው በስደት የሚመጡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ማረጋጊያና ማጠንከሪያ የምክር አገልግሎቶችን የሚያገኙበት፣ ከሀገሩ ባሕል፣ ቋንቋና አስተዳደር ጋር በአግባቡ የሚተዋወቁባቸው ሥልጠናዎች የሚሰጥበት፣ በአካባቢው ተወልደው የሚያድጉ ሕጻናት ስለሀገራቸውና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸው ታሪክ፣ ቋንቋና ባሕል የሚያውቁበት፣ የቤተ ክርስቲያኗ ዕውቀት፣ ባሕልና ትውፊት ጥናት የሚደረግበት፣ ቋሚ ዐውደ ርእይን ጨምሮ በልዩ ልዩ መልኩ የሚቀርብበት እንዲሆን ታስቧል።

ክቡራንና ክቡራት ኦርቶዶክሳውያን፤

የዚህ ተቋም መመሥረት አስፈላጊነት ተኑሮ የሚታይ እንጂ በቃላት ሊገለጽ የሚችል አይደለም። በመኾኑም እኛ በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የምንገኝ ማኅበረ ካህናትና ምእመናን “እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ በርቱና ሥሩ ይላል እግዚአብሔር። እኔ ከእናንተ ጋ ነኝና ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” (ሐጌ 2፤4-8) ያለን አምላክ አጋዥነት ተማምነን፤ ከሀገረ ስብከቱ አልፎ በመላው ዓለም የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን አበውንና ምእመናንን ትብብር በማመን ይህንን ቦታ ለመግዛት እንቅስቃሴ ጀምረናል። በመኾኑም በሀገረ ስብከታችንና በመላው ዓለም የምትገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ወደፊት በየአካባቢያችን በሚዘጋጁ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ጉባኤያት፣ በሚላኩን ገንዘብ መለገሻ መንገዶች ኹሉ የእርዳታ እጃችኹን በመለገስ ይህንን በዘመናችን ተጽፎ በሚመጣው ትውልድ ሲዘከር የሚኖር ታሪክ በጋራ እናስቀምጥ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ቃሉ በዓለም ይሰበክ ዘንድ ለአባቶቻችን ጥበብንና ጽናትን የሰጠ አምላክ ለእኛም ሰጥቶ እንዲያስፈጽመን በጸሎታችኹ አስቡን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል፤ አሜን።

በኢ.ኦ.ተ.ቤ. የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት


አባ ዲዮናሲዮስ
Halbauer Weg 15
12247 Berlin
Tel: +4915901853171
Donate

Donations 

    Donate

    Organizer

    Verband der ÄOT Kirchen Erzdiözese von Deutschland und Umgebung e V
    Organizer
    Frankfurt, Hessen

    Your easy, powerful, and trusted home for help

    • Easy

      Donate quickly and easily

    • Powerful

      Send help right to the people and causes you care about

    • Trusted

      Your donation is protected by the GoFundMe Giving Guarantee